ሰኔ 12 የቅዱስ ሚካኤል በዓል ወረብ | Sene Mikael Wereb | በመምህር ፍሬ ስብሐት መንገሻ | አ.አ. | መናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ
ማኅሌት Mahlet ማኅሌት Mahlet
2.15K subscribers
9,624 views
188

 Published On Jun 18, 2020

#እንኳን_ለቅዱስ_ሚካኤል_በዓል_በሰላም_አደረሳችሁ፡፡
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
እነሆ ይህች ዕለት ለቅዱሳን መላእክት አለቃቸው የሆነ፣ የስሙ ትርጓሜ "ማን እንደ አምላክ" የሆነ፣ የመልአከ ምሕረት ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል በዓለ ሢመት ዓመታዊ መታሰቢያ ናት፡፡ ፈጣሬ ዓለማት ልዑል እግዚአብሔር ዕፁብ ድንቅ በሆነ በማይመረመር ጥበብ ፍጥረታትን ከፈጠረባቸው ስድስት ዕለታት በመጀመርያዪቱ ዕለት በእሑድ መላእክትን ከፈጠራቸው በኋላ በተሰጣቸው አእምሮ ይመራመሩ ዘንድ ተሠወራቸው፡፡ ታድያ ይህን ጊዜ በመላእክት ዓለም ሁከት ተነሣ፤ ማን እንደፈጠራቸው አላወቁምና፡፡ ሳጥናኤልም ከወደ በላዩ ተመለከተ፤ ከእርሱ በላይ የሆነ ማንንም አላገኘም፡፡ ወደ ታችም ተመለከተ፤ እልፍ አእላፋት መላእክት ፈጣሪያቸው ማን እንደሆነ እየጠየቁ ነው፡፡ ይህን ጊዜ ነበር "እኔ ፈጠርኋችሁ" ብሎ የመጀመርያውን የሐሰት ንግግር የተናገረው፡፡ በሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል "ባለንበት እንጽና" ድንቅ ቃል ዘጠና ዘጠኙ ነገደ መላእክት ጸንተው ሲቆሙ በሳጥናኤል ነገድ ግን ክሕደት በርክቶ ነበር፡፡ ታዲያ ይህች ቀን ቅዱስ ሚካኤል ዲያቢሎስን ተዋግቶ ያሸነፈባት፣ የማይገባውን አምላክነትን ሽቶ በወደቀው በከሐዲው ዲያቢሎስ ምትክ ከወገኖቹ ከመላእክት ሁሉ በላይ ሆኖ በሁሉ ቅዱሳን መላእክት ላይ ከልዑል እግዚአብሔር ከክብሩና ከገናናነቱ ጋር ሹመትን ያገኘባት ታላቅ ዕለት ናት፡፡ ሹመቱም በአንድ ነገድ ላይ ብቻ አይደለም፤ በሁሉ የመላእክት ነገድ ላይ እንጂ፡፡ እርሱም በመንፈሳዊ ሕይወት የደከሙትን የሚያበረታ፣ አርምሞ ትዕግሥትን የሚወድድ፣ ለፍጥረታት ሁሉ የሚራዳና የሚያዝን፣ የምሕረትና የመዳኛ፣ የሰላም መልአክ ትሑትና ርኅሩኅ ነው፡፡ ዳግመኛም ይህች ዕለት ንዕድ ክብርት የሆነች ቅድስት አፎምያ የዕረፍቷ መታሰቢያ ናት፡፡ ቅድስት አፎምያ አንድ ሃይማኖቱ የቀና እግዚአብሔርንም የሚፈራ ስሙ አስተራኒቆስ የተባለ ታላቅ መኰንን ሚስት ነበረች፡፡ ባሏ አስተራኒቆስ ለምስኪናን ምጽዋትን የሚሰጥ፣ በየወሩም ሦስት ጊዜ በዓላትን የሚያከብር ደግ ሰው ነበር፡፡ እነዚህም በዓላት ወር በገባ በ፲፪ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል፣ በ፳፩ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም እና በ፳፱ የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደቱ መታሰቢያ በዓላት ናቸው፡፡ ታዲያ በአንድ ወቅት ይህ ሰው ታመመ፤ የሚሞትበት ጊዜም ደረሰ፡፡ ይህን ጊዜ ሚስቱን አፎምያን እርሱ በሕይወት ዘመኑ ያደርገው የነበረውን መመጽወትን እንዳታስቀር ነገራት፡፡ የበዓላቱን መታሰቢያም አታስታጕል ዘንድ አደራ አላት፡፡ እርሷም ባሏን፣ በቤቷ አኑራ ከሰይጣን ፈተና ትከላከልበት ዘንድ የሊቀ መላእክት የቅዱስ ሚካኤልን ሥዕል አሥሎ ይሰጣት ዘንድ ጠየቀችው፤ እርሱም ይህን ካደረገላት በኋላ ዐረፈ፡፡ ከባሏ ማረፍ በኋላ ቅድስት አፎምያ እርሱ ይሠራው ከነበረው በጎ ሥራ ሁሉ አንዳች ሳታጓድል እየሠራች በሃይማኖት ጸንታ ትኖር ጀመር፡፡ የክፋት አባት የሆነው ዲያቢሎስም በጎ ምግባሯን ባየ ጊዜ በቅንዓት ተነሣባት፤ በብዙም ፈተናት፡፡ በመበለት መነኰሳይት ተመስሎ እየመጣ በጣም እንደሚያዝንላት፣ ዕድሜዋ ሳያልቅ ገንዘቧም በምጽዋት ከማለቁ በፊት ብታገባና ልጆች ወልዳ ብትኖር እንደሚሻል ይመክራት ጀመር፡፡ ቀጥሎም፤ "ባልሽ እንደሆነ መንግሥተ ሰማያትን ወርሷል ምጽዋትን አይፈልግም፡፡" ብሎ ሊያሰናክላት ሞከረ፡፡ እርሷ ግን፤ "ከእንግዲህ ከሌላ ወንድ ጋር ላልገናኝ ለእግዚአብሔር የመሐላ ቃሌን ሰጥቻለሁና አላደርገውም፡፡" ብላ መለሰች፡፡ "ርግቦችና ቁራዎች ስንኳ ባላቸው ከሞተ ሌላ ባል አያውቁም፡፡ በአርአያ እግዚአብሔር ለተፈጠሩ ሰዎችማ ይህን ማድረግ እንዴት ይገባል?" አለችው፡፡ ምንም ያህል ቢጥርም እንኳን ነገሩን እንዳልተቀበለችው ባየ ጊዜ መልኩን ለውጦ ዛሬ ባይቻለውም እንኳን በሌላ ቀን መጥቶ ሃሳቡን እንድትቀበል እንደሚያደርጋት በመናገር ጮኸ፤ በቅዱስ ሚካኤል ሥዕል ኀፍረትን አከናንባ አዋርዳ አጠፋችው፡፡ በሰኔ ፲፪ በሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ክብረ በዓል ቀን ዲያቢሎስ ዳግመኛ ሊፈትናት ብርሃናዊ መልአክ መስሎ የብረት ዘንግ ይዞ በሌሊት ወደ እርሷ መጣ፡፡ ስለ በጎ ሥራዎችዋ ስለ መልካምነቷ ከክፉ እንዲጠብቃት ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልኮ እንደመጣ ነገራት፡፡ ስሙን ብትጠይቀው የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል እንደሆነ ዋሽቶ ነገራት፡፡ "እነሆ ገንዘብሽን በምጽዋት ማባከንሽን ትተሸ ከምእመናን ወገን ለአንዱ ሚስት ትሆኚ ዘንድ እግዚአብሔር ወደ አንቺ ልኮኛል፡፡ በዚህም ላይ ያለ ባል የምትኖር ሴት መቅዘፊያ እንደሌላት ወይም መልሕቅዋ እንደተቆረጠ መርከብ መሆንዋን ዕወቂ፡፡" አላት፡፡ ከብሉይ መጻሕፍት እነ አብርሃም፣ ይስሐቅ፣ ያዕቆብ ፣ ዳዊትን እያነሣ ያገቡ ነገር ግን የእግዚአብሔር ባለሟሎች የነበሩ መሆናቸውን ጠቅሶ ማግባት እንዳለባት ነገራት፡፡ ቅድስት አፎምያም መልሳ በእውነት የእግዚአብሔር መልአክ ከሆነ የመታወቂያው ምልክት የሚሆን ትእምርተ መስቀሉ ወደየት እንዳለ ጠየቀችው፡፡ እርሱም፤ "በእኛ በመላእክት ዘንድ እንዲህ ያለ ምልክት የለም፡፡" አላት፡፡ በእጅጉ ስለተጠራጠረችው ባሏ ከመሞቱ በፊት አሠርቶ የሰጣትን የሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤልን ሥዕል ልታመጣ ወደ ሥዕል ቤቷ ሔደች፡፡ ይህን ጊዜ ዲያቢሎስ መልኩ ተለወጠ፤ ዘልሎም አነቃት፡፡ ቅድስት አፎምያ ወደ ቅዱስ ሚካኤል እንዲያድናት እየጮኸች ለመነች፡፡ ለመልካም ሥራ የሚፋጠን መልአከ ኃይል ቅዱስ ሚካኤልም መጥቶ አዳናት፡፡ ሰይጣኑንም በብዙ ሥቃይ አሠቃየው፡፡ ሰይጣኑም እግዚአብሔር የሰጠው ዘመኑ ሳይፈጸም አያጠፋው ዘንድ ቅዱስ ሚካኤልን ተማፀነው፤ ያን ጊዜም ተወው፡፡ ከዚህ በኋላም የቅድስት አፎምያ የዕረፍቷ ቀን ደርሷልና ቅዱስ ሚካኤል ሔዳ ቤቷን ታዘጋጅ ዘንድ ነገራት፡፡ "በዛሬው ዕለት ከዚህ ዓለም በሞት ትለያለሽ፡፡ እነሆ እግዚአብሔርም ዐይን ያላየውን ጆሮ ያልሰማውን ልቡና ያላሰበውን ዋጋሽን አዘጋጅቶልሻል፡፡" ብሎ ከነገራት በኋላ ሰላምታ ሰጥቷት ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡ እርሷም ለበዓሉ የሚያስፈልገውን ከአዘጋጀች በኋላ ወደ ኤጲስ ቆጶሱ እና ካህናቱ ዘንድ መልእክተኛ ላከች፤ ቀጥሎም በእነርሱ እጅ ለነዳያንና ለችግረኞች ምጽዋትን ይሰጡላት ዘንድ ገንዘብን ሰጠች፡፡ ከዚህም በኋላ የቅዱስ ሚካኤልን ሥዕል በደረቷ እና በፊቷ ላይ አድርጋ ወደ እግዚአብሔር እየጸለየች የቅዱስ ሚካኤል በዓል በሚከበርበት ዕለት በሰኔ ፲፪ ቀን በክብር ዐረፈች፡፡ አምላከ አማልክት ልዑል እግዚአብሔር ከክፉ ዲያቢሎስ እጅ ያስጥላት ዘንድ ቅዱስ ሚካኤልን ወደ ቅድስት አፎምያ እንደላከ እኛንም በፈተናዎቻችን ሁሉ ይረዳን ዘንድ ከቅዱስ ሚካኤል ረድኤት በረከት ይክፈለን፡፡ አሜን፡፡ ይቆየን……. ወስብሐት ለእግዚአብሔር

show more

Share/Embed