ግንቦት 11 የቅዱስ ያሬድ በዓለ ስዋሬ ወረብ | Kidus Yared Wereb | በመምህር ፍሬ ስብሐት | አ.አ | መናገሻ ገነተ ጽጌ
ማኅሌት Mahlet ማኅሌት Mahlet
2.15K subscribers
6,797 views
167

 Published On May 19, 2020

#ማኅሌቱን_ለማኅሌት_አባት_እናቅርብለት::
#እንኳን_ለቅዱስ_ያሬድ_በዓለ_ስዋሬ_በሰላም_አደረሳችሁ::
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
"አልቦ እም ቅድሜሁ ወአልቦ እም ድኅሬሁ ማኅሌታይ ሰብእ ዘከማሁ---ከእርሱ በፊት ከእርሱም በኋላ እንደ እርሱ ያለ ማኅሌታይ ሰው የለም፡፡"
ለቤተክርስቲያናችን ድምፅን የሚያሰማ ቀርን፣ ሃይማኖትን የሚመግብ ወንጌልን የሚሰብክ የኢትዮጵያ ፀሐይ የተባለው ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ከእናቱ ታውክልያ (ክርስቲና) እና ከአባቱ አብዩድ (ይስሐቅ) በሚያዝያ ፭ ቀን ፭፻፭ ዓ.ም በአክሱም ተወለደ፡፡ በተወለደ በ፯ ዓመቱ አባቱ በመሞቱ እናቱ ዜና ገብርኤል ለተባለ ሰው አገልጋይ ይሆን ዘንድ ሰጠችው፡፡ እርሱም ቅዱስ ያሬድ ገና ሕጻን ስለነበር "አያገለግለኝም" ብሎ ለእናቱ መልሶ ሰጣት፡፡ ከዚህም በኋላ እናቱ ክርስቲና የአክሱም ጽዮን ቤተክርስቲያን ገበዝ ለነበረው ለአጎቱ ለአባ ጌዴዎን እያስተማረ ያሳድገው ዘንድ ወስዳ በአደራ ሰጠችው፡፡ ያሬድም ከአባ ጌዴዎን እየተማረ ተቀመጠ፡፡ ነገር ግን ትምህርት አልገባ ብሎት ለብዙ ዓመታት ያህል ደከመ፡፡ ከዕለታት በአንድ ቀን ከትምህርቱ ድክመት የተነሣ አጎቱ ጌዴዎን፤ "ተግተህ ተማር" ብሎ በጭንገር ገረፈው፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር ቅዱስ ያሬድ ተበሳጭቶ ትምህርቱን ትቶ ወደ መደባይ ወለል (እናቱ ወዳለችበት) ቦታ ለመሔድ ጉዞ የጀመረው፡፡
በመንገድ ላይ ሳለ ቀትር ላይ ደከመውና "ማይ ኪራህ" በተባለች ቦታ ኪሬህዋህ ከተባለች ዛፍ ጥላ ሥር ዐረፍ አለ፡፡ በዚያም ሕይወቱን የለወጠ አንድ ምሳሌን ዐየ፡፡ ይኸውም አንዲት ትል ከዛፍ ላይ ያለውን ፍሬ ለመብላት ፮ ጊዜ ወጥታ ፍሬውን ስትበላ ተመለከተ፡፡ ያቺ ደካማ ትል ስትወድቅ ስትነሣ ቆይታ ኋላ ግን ፍሬውን መብላቷን ሲመለከት ተጸጸተ፡፡ ወደ አጎቱም ተመልሶ ይቅርታን ጠየቀ፤ ትምህርቱንም ቀጠለ፡፡ አጎቱም በቅዱስ ያሬድ መመለስ ተደስቶ ልቦናውን ያበራለት ዘንድ ፈጣሪውን ለመነለት፡፡ የለመኑትን መልካሙን ሁሉ የማያሳጣው እግዚአብሔር አምላክም ጸሎቱን ሰምቶት ለቅዱስ ያሬድ ዕውቀትን ገልጦለት አእምሮውን ከፍቶለት የብሉይ ኪዳን እና የሐዲስ ኪዳን ፹፩ መጻሕፍትን በአንድ ጊዜ ፈጽሞአል፡፡ በተለይም ቅዱስ ያሬድ መዝሙረ ዳዊትን እየተማረ ሳለ እግዚአብሔር የልቡን ቅንነት የሃይማኖቱን ጽናት ዐውቆ መዝሙረ ዳዊትን፣ መኃልየ ነቢያቱን፣ ወመኃልየ ሰሎሞኑን፣ ቅዱስ ኤፍሬም የደረሰውን ውዳሴ ማርያምን የሰማንያ አንዱን ትርጓሜ ቅዱሳት መጻሕፍት በአጠቃላይ መጻሕፍተ ሐዲሳትን ጠንቅቆ ዐወቀ፡፡
ቅዱስ ያሬድ የተገለጡለትን ቅዱሳት መጻሕፍት በቃሉ ይዞ በመምህሩ በአባ ጌዴዎን ዘንድ ሆኖ ሲያስተምር የትምህርቱ ጽናት፣ ደግነቱና ትዕግሥቱ፣ ትሕትናውና ፍጥነቱ በመምህሩና በሕዝቡ ተመስክሮለት የአክሱም ጽዮን ሊቀ ኤጲስ ቆጶስ የነበሩ አባ ዮሐንስ መዓርገ ዲቁናን ሰጡት፤ አከበሩትም፡፡ መምህሩ አባ ጌዴዎን በሞት ሲለዩም የእሳቸውን ቦታ ተክቶ ብሉያቱንና ሐዲሳቱን ከፋፍሎ በማስተማር እስከ ፭፻፴ ዓ.ም ድረስ ቆይቶ ብዙ ሊቃውንትን አስገኝቶአል፡፡
ቅዱስ ያሬድ በአክሱም ጽዮን ቤተክርስቲያን እያገለገለ ሳለ በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ቀደም ሲል በንባብና በለኆሣስ ይዘመር ስለነበር እግዚአብሔር በዜማ መመስገን ፈቃዱ ስለሆነ ቅዱስ ያሬድን ምክንያት አድርጎ ከ፳፬ቱ ካህናተ ሰማይ በሥላሴ ምሳሌ ግእዝ፣ ዕዝል፣ አራራይ የሚባሉ ሦስት ዜማዎችን አስተምሮታል፡፡ ግእዝ የመጀመርያ (ደርቅ) ዜማ ይባላል፤ ምሳሌነቱ ለአብ ነው፡፡ ዕዝል ታዛይ ተደራቢ ማለት ነው፡፡ ከግእዝ ጋር ተደርቦ የሚተዛዘል ዜማ ነው፡፡ አሳዛኝ ዜማ ይባላል፡፡ ይህ ዜማ የወልድ ምሳሌ ነው፡፡ አራራይ ማለት ደግሞ የሚያራራ ማለት ነው፤ ምሳሌነቱ ለመንፈስ ቅዱስ ነው፡፡
ቅዱስ ያሬድ ኅዳር ፭ ቀን ከጠዋቱ ፫ ሰዓት ላይ ከኤደን ገነት ሦስት መላእክት በወፍ አምሳል ተገልጠው፤ "አንተን ያጠቡ ጡቶች የተባረኩ ናቸው፡፡" አሉት፡፡ ከዚያም እነዚያ ከገነት የመጡ አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ቀለም ያላቸው ሦስት አዕዋፍ ካስተማሩት በኋላ ወደ ሰማያዊት ኢየሩሳሌም በተመስጦ ተጉዞ ከዚያ የቅዱሳን መላእክትን ዜማ ዐይቶና ሰምቶ ከሰማያዊት ኢየሩሳሌም ኅዳር ፮ ቀን ተመለሰ፡፡ እንደተመለሰም ሙራደ ቃል (የቃል መውረጃ) በተባለ ቦታ የዜማው መጀመርያን ዘመረ፤ "ሃሌሉያ ለአብ ሃሌሉያ ለወልድ ሃሌሉያ ለመንፈስቅዱስ ቀዳሚሃ ለጽዮን ሰማየ ሣረረ ወለዳግም አርአየ ለሙሴ ዘከመ ይገብር ግብራ ለደብተራ---ዓለም ሳይፈጠር ለነበረና ዓለምን አሳልፎ ለዘለዓለም ለሚኖር ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይገባል፡፡ የጽዮን ፈጣሪ እግዚአብሔር አምላክ በመጀመርያ ሰማይን ፈጠረ፡፡ ሁለተኛ ደብተራ ኦሪትን እንዴት አድርጎ መሥራት እንደሚችል ለሙሴ አሳየው፡፡" የሚል ዜማ ነበር፡፡ ይህችንም የመጀመርያውን ዜማ "ዜማ አርያም" አላት፤ ይኸውም ከሰማይ የመጣች ስለሆነች ነው፡፡ በአራራይ ዜማ አዚሞአታል፡፡
ይህንኑ ድርሳነ ዜማ በጊዜው የነበረው ንጉሥ ገብረ መስቀል በሰማ ጊዜ ጫማውን ሳይጫማ ንግሥቲቱም ደንገጡሮችዋን አጃቢዎችዋን ሳታስከትል መኳንንቱ፣ ካህናቱና መምህራኑ እነርሱን ተከትለው እየተጣደፉ ወደ ዐደባባዩ በመሔድ በተመስጦ ሲሰሙት ውለዋል፡፡ ከዕለታት በአንዳቸው በዐቢይ ጾም ጊዜም ቅዱስ ያሬድ በተመስጦ ልዑል እግዚአብሔርን በዝማሬ ሲያመሰግን ንጉሥ ገብረ መስቀል ሳያውቁት ልባቸው በጣዕመ ዜማው በመመሰጡ የብረት ዘንጉን በቅዱስ ያሬድ እግር ላይ ተከሉት፡፡ ቅዱስ ያሬድ ግን ምንም እንኳን ከእግሩ ደም እየፈሰሰ ቢሆንም የሚያዜመው በተመስጦ ነበርና ማኅሌቱን እስኪፈጽም ድረስ ምንም አልተሰማውም ነበር፡፡ በጨረሰም ጊዜ ንጉሡ የደሙን መፍሰስ ዐይቶ ደነገጠ፡፡ ቅዱስ ያሬድንም፤ "የደምህ ዋጋ የፈለግኸውን ንገረኝ" አለው፡፡ ቅዱስ ያሬድም ምኞቱ ወደ ገዳም መሔድ ነበርና ሔዶ ይመነኵስ ዘንድ እንዲፈቅድለት እንደሚፈልግ ነገረው፡፡ ይኸውም ቅዱስ ያሬድ በመኳንንቱ በሕዝቡ ሁሉ እየታወቀ እየተደነቀ ነበርና ውዳሴ ከንቱ አያጠቃው ዘንድ ነው፡፡ ንጉሡም ይህን በሰማ ጊዜ እጅግ አዘነ፡፡ ነገር ግን ምንም ቢጠይቅ ሊያደርግለት ቃል ገብቶ ነበርና ፈቀደለት፡፡
ቅዱስ ያሬድም በአክሱም ጽዮን ማርያም ገብቶ አለቀሰ፡፡ እመቤታችንም ተገልጣ፤ "ሰማያዊት ኢየሩሳሌምን ያስመሰልካት ቤተክርስቲያኔን የት ነው ትተህ የምትሔደው?" አለችው፡፡ እርሱም በጸሎት በምናኔ መኖርን እንደሚፈልግና እንድትፈቅድለት ጠየቃት፤ ፈቀደችለትም፡፡ የአንቀጸ ብርሃንን ምስጋና ከመጀመርያው እስከ መጨረሻው በተናገረ ጊዜ በእግዚአብሔር ኃይል ክንድ ያህል ከምድር ከፍ ከፍ አለ፡፡ ከዚያም ወደ ዝዋይ ሔደ፡፡
ከዚህም በኋላ ወደ ሰሜን ተራሮች ሔዶ ጸለምት ወደ ተባለች ቦታ ወጥቶ ብርድ በጸናበት በረዶ በተከማቸበት ካኔር በተባለ ቦታ ጉባኤ ዘርግቶ ማስተማር ጀመረ፡፡ በዚያም ከ፳፪ ዓመታት በላይ ቆይቶአል፡፡ በሰሜንና ወገራ አገው በጌምድር እየተዘዋወረ ካስተማረ በኋላ በሰሜን ተራራዎች ሥር ካሉ ገዳማት በአንዱ ዋሻ ውስጥ እየጾመ እየጸለየ በብሕትውና በምናኔ ታግሦ ብዙ ዘመን ከኖረ በኋላ በ፭፻፸፩ ዓ.ም ግንቦት ፲፩ ቀን በደብረ ሐዊ ቅዱስ ያሬድ ገዳም ተሠውሮአል (አርፎአል)፡፡
ቅዱስ ያሬድ ከእርሱ በፊት በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የተወሰነ ደንበኛ የቅኔና የዜማ ትምህርት ስላልነበረ ከብሉይ እና ከሐዲስ ኪዳን ከሊቃውንት መጻሕፍት እያውጣጣ ደንበኛ የዜማ ስልትን አዘጋጅቷል፡፡ የድርሰት ሥራዎችን ፤ድጓ(ጾመ ድጓ የዚህ ክፍል ነው)፣ ምዕራፍ (አንቀጸ ብርሃን ከዚህ የወጣ ነው)፣ ዝማሬ፣ መዋሥዕትን አዘጋጅቶአል፡፡ ለዜማውም ድፋት፣ ሒደት፣ ቅናት፣ ይዘት፣ ቁርጥ፣ ጭረት፣ ርክርክ፣ ደረት፣ የተባሉ ፰ የዜማ ምልክቶችን አዘጋጅቶአል፡፡ ዜማዎቹን በ፬ ከፍሎ በክረምት፣ በበጋ፣ በመፀው እና በጸደይ ወራት ከሚከሠቱ ተፈጥሮአዊ ሁኔታዎች ጋር እያስማማ አዘጋጅቶአል፡፡ በተለያዩ ሊቃውንት የተደረሱትን ዐሥራ አራቱንም ቅዳሴያት በዜማ ባማረ መልክ ያዘጋጀው ቅዱስ ያሬድ ነው፡፡ በትርጓሜ ቅዳሴ ማርያም ላይ እንደምናነበው ቅዱስ ያሬድ ማይ ኪራህ በተባለው ቦታ ተሠውሮ ጸዋትወ ዜማን ሲያስተምር እመቤታችን ሶርያዊው ቅዱስ ኤፍሬምን እና የብህንሳውን አባ ሕርያቆስን በአካለ ነፍስ እንዲመጡ አድርጋ ኤፍሬም ውዳሴዋን ሕርያቆስ ቅዳሴዋን እየነገሩት እርሱ በዜማ እንዲያደርስ አድርጋዋለች፡፡
ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ቅዱስ ያሬድን፤ "የመንፈስ ቅዱስን ምግብ የጠገበ፤ ከመጻሕፍት ሁሉ ትርጓሜያተ ድርሰትን ያሰባሰበ፤ ሃሌሉያ በሚል ምስጋና ኢትዮጵያ ሀገርን በጥዑም ማኅሌትና በሚያምር ምስጋና ያስጌጠ፤ የመለኮት ቃልን በላይዋ ላይ እንደ ንጹሕ የወርቅ ሻሻቴ ያፈሰሰ ለሆነ ለካህኑ ያሬድ ሰላምታ ይገባል፡፡" ሲል ያወድሰዋል፡፡ እኛም በዚህች በተሠወረባት ዕለት ስሙን እያወደስን ለእርሱ የሰማያውያንን ምሥጢር የገለጠ አምላክ ለእኛም ከእርሱ በረከት ያሳትፈን ዘንድ እየለመንን እያመሰገንን እንውላለን፡፡ የቅዱስ ያሬድ ረድኤቱ በረከቱ አይለየን፡፡ አሜን፡፡ ይቆየን…
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

show more

Share/Embed